የሰው የሙያ ዘርፍ የሚሠማራበት
አይነቱ ብዙ ነው የማያልቅ ቢቆጥሩት
ነገር ግን እንዲሁ ያለምንም ጥናት
ወይ የአዕምሮ ሥራ አልያም የጉልበት
ብለን በመለየት የምንመደብበት
ቀለል ያለ መስፈርት አስበን በማውጣት
ሙያዎችን ሁሉ አንድ በአንድ በማየት
ይመስለኝ ነበረ ከሁለቱ አንዱ ውስጥ የሚቻል ማጸተት
ግልጽ እስኪሆንልኝ አንድ ቀን በድንገት
እንዳስብ አድርጎኝ ያልጠበኩት ክስተት
በሩቁ የማውቀው ከአመታቶች በፊት
ጊዜው በመርዘሙ አሁን የረሳሁት
አንድ ሰው በመንገድ ስላየኝ በርቀት
ፈጠን ብሎ መጥቶ እኔ ወደአለሁበት
የትና መቼ ነው ይህን ሰው ያየሁት
ወይስ እውቅና አለን በሚል አይነት ስሜት
ከጎኔ እየሄደ በስርቆሽ እያየኝ የማላየው መስሎት
ትዝ አልልህ ሲለው ጊዜውና ቦታው እኔን የሚያውቅበት
ይቅርታ ወንድሜ አንዴ ላናግረዎት
ብሎ ሳላስበው አስቁሞኝ በድንገት
መድፈር ባይሆንብኝ ወይም ባልሳሳት
ቅድም በመንገድ ላይ በሩቁ ሳይዎት
እርግጠኛ ነበርኩ እነደተገናኘን ከዛሬ ቀን በፊት
ማስታወስ ባልችልም የት እንደማውቀዎት
ብሎ የእኔን ምላሽ ሲጠብቅ በጉጉት
ግራ ተጋብቼ በሰውዬው ድርጊት
ምንም ሳልናገር አትኩሬ እያየሁት
እኔ አላስታውስም ብዬ በምልክት
እርግጠኛ ሆኜ መልሴን ሳቀርብለት
ድንገት ፈገግ ሲል በመገረም ስሜት
በፍንጭት ጥርሶቹ ማን እንደሁ አወቅሁት
ከዚያም ብዙ ሳልቆይ ይቅርታ ጠይቄው ለሰራሁት ስህተት
አንድ ሰፈር ስንኖር ከ ሀያ አመት በፊት
ከ እግዚአብሄር ሰላምታ ያለፈ ባይሆንም የነበረን ቅርበት
በከተማችን ውስጥ በዚያን ወቅት ታዋቂ ናቸው ከሚባሉት
አንዱ እንደነበረ በደንብ ማስታወሴን አረጋግጨለት
ከዚያም በመቀጠል ስለትዝታችን በደንብ ለመጫወት
ቡና እንጠጣ ብዬ ግብዣ አቀረብኩለት
እሱም በሀሳቤ ስለተስማማበት
ተያይዘን ገብተን ወደ አንድ ቡና ቤት
ስለ ብዙ ነገር አንስተን ተጫውተን ለረዥም ሰአታት
በስተመጨረሻ ሆነ ብዬ ሳይሆን ለማወቅ በመሻት
እሱን ያስቀይማል ብዬ ያላሰብኩት
ከሌሎች ሰዎች ጋር ያኔ የነበረው ቅርብ ግንኙነት
ለምን የሻከረ ሊሆን እንደቻለ ድንገት ሳነሳበት
መልሶ አፋጠጠኝ ጥያቄዬን በደንብ ግልጽ እንዳደርግለት
እኔም ኮስተር ብዬ አትኩሬ እያየሁት
ማወቅ የምሻውን እንደሚከተለው አድርጌ አስረዳሁት
ለእሱ ብዙ ሰዎች ለምን እንዳላቸው መጥፎ አመለጸከት
ለማወቅ በማሰብ ያኔ እንዳደረብኝ ከፍተኛ ጉጉት
ነገር ግን ሚስጢሩን እስከዛሬ ድረስ እንዳልተረዳሁት
አሁንም ለማወቅ ፍላጎት እንዳለኝ ግልጽ ሳደርግለት
ሲለወጥ አየሁት ፊቱ ከመቅጽበት
በጣም መረበሹ እስኪታወቅበት
ድንብርብሩ ወጥቶ ምላሱ ተይዞ መናገር አቅቶት
አብረን እንደነበርን ጭራሹን እረስቶት
ጊዜ እንኳን ሳይሰጠኝ ይቅርታ ለማለት
ወይም ለመጠየቅ ምን እንዳስቀየምኩት
ስርአት ባለው መንገድ ሳንሰነባበት
ጥሎኝ ወጥቶ ሄደ ሮጦ በፍጥነት
ጭራሽ ያልጠበኩት ይህ እንግዳ ድርጊት
ይበልጥ ገፋፋኝ ማወቅ እንዳለብኝ ስለዚያ ሰው ህይወት
ከዚያም ሳሰላስል ጠቃሚ መረጃ ስለማገኝበት
አንድ ሰው ትዝ አለኝ የማውቀው በቅርበት
ከዚያ ሰው ጋር ዱሮ በደንብ የነበረው ጥብቅ ጓደኝነት
በመጣልኝ ሀሳብ በጣም በመደሰት
ጊዜ ሳላጠፋ ለዚህ ለማውቀው ሰው ስልክ ደውዬለት
አንድ ምግብ ቤት ውስጥ ማታ እንድንገናኝ ቀጠሮ ሰጠሁት
ቀጠሮው ቦታ ላይ ቀድሜው ደርሼ ከስአቱ በፊት
ሰዎች ሳይረብሹን ተዝናንተን ለማውራት
አመቺ ያልኩትን ጠረጴዛ ይዤ ስጠብቅ በጉጉት
በአጋጣሚ አየሁት ቀጥ ብሎ ሲመጣ እኔ ወደአለሁበት
አጠገቤም ሲደርስ እንኳን ደህና መጣህ ብዬ ተቀበልኩት
ከዚያም በመቀጠል እራት እንድንበላ ግብዣ ሳቀርብለት
ግብዣዬን በደስታ ወዲያው ተቀብሎት
እራት እየበላን ብዙ ስንጫወት
የድሮ ጓደኛው ስለነበረው ሰው ድርጊት አንስቼበት
የሆነውን ሁሉ አንዱንም ሳላስቀር በደንብ ገልጨለት
ለምን እንደሆነ እንደዚያ የሆነው ጥያቄ ጠየኩት
እሱም አፍጥጦብኝ በመገረም ስሜት
ለምን እንደሆነ አልገባህም በእውነት?
ወይስ በዚህ እድሜህ ጀምረሀል መርሳት?
በእርግጥ አታውቀውም የዚህን ሰው ሙያ የሥራውን አይነት?
ለምን ይመስለሀል ማንነቱን እንኳን ጭራሽ የማያውቁት
ሙያውን ሲሰሙ ከሩቅ የሚሸሹት?
ብሎ ሲያጣድፈኝ በጥያቄ ብዛት
በእውነት እመነኝ ምን እንደሚሠራ እኔ አላውቅም አልኩት
መልሴን እንደሰማ ትንሽ አስቦበት
ሙያው ልንገርህ አድምጠኝ በንቃት
ብሎ ጊዜ ወስዶ አስረዳኝ በስፋት
የወሬ ንግድ ነው ይህ ሰው እንደ ሙያ የተሰማራበት
ወሬን ተቀብሎ ወሬን ማሰራጨት
ሰዎች የሚሉትን በስውር በመስማት
ምንም ሳይጣራ እውነት ይሁን ሀሰት
በእራስ መንገድ አይቶ ልዩ ትርጉም መስጠት
ይህን ግርድፍ ግኝት ለፈለጉት ተግባር እንዲጠቀሙበት
እውነት አስመስሎ አሳልፎ ሰጥቶ ለሌሎች አጸላት
ሰዎችን በወሬ ወንጀለኛ አድርጎ መቀመቅ ውስጥ መክተት
ይህን ሲሰራ ነው ከምትለው ሰው ጋር ያኔ የተዋወቅኩት
ከዚያም በአጭር ጊዜ ለመፍጠር የቻልነው ቅርብ ግንኙነት
እሲኪቋረጥ ድረስ ጓደኝነታችን ቀስ በቀስ በሂደት
ይህ የምትለው ሰው ያኔ የሚኮራበት
አሁን ግን በእጅጉ ከልብ የሚያፍርበት
ያ የዱሮ ሙያው አጋልጦ ጥሎታል ለዘለአለም ጭንቀት
ብሎ እንደጨረሰ ጉዳዩን ማስረዳት
ክርክር ጀመርኩኝ ከእራሴ ጋር ሙግት
ይሄን ልዩ ሙያ በሰከነ መንፈስ ሳጠናው በጥልቀት
የአዕምሮው ሥራዎች አልያም የጉልበት ተብለው ከተለዩት
ከሁለቱ አንዱ ውስጥ ልመድበው ብዬ ብዙ ባስብበት
በፍጹም አልቻልኩም ተስማሚ የሆነ ቦታ ላገኝለት
እነማን ምን አሉ ፣ ከእነማን ጋር ዋሉ
የት የት ይሄዳሉ ፣ ማንን ያገኛሉ
ምን ምን ተባባሉ ፣ ምንስ ያስባሉ
ብሎ እየጠየቀ ነገር የሚለቅም
ወሬኛ ነው እንጂ ሠራተኛ አይደለም