ኑሮ እጅግ ተወዶ አልቀመስ ብሎን
ጠግበን የምናድር አልመስል እያለን
በጣም ስንጨነቅ ስለ እለት ጉርሳችን
የሆዳችን አንሶ ልብሳችን ሲያልቅብን
የምንጨብጠው የምንይዘው አጥተን
ምን እንደምናደርግ ግራ ግብት ብሎን
ወደድንም ጠላንም የምንበላውን ማስቀደም አለብን
ሆዳችን ከሞላ መሄድ እንችላለን ቀዳዳ ልብስ ለብሰን
ብለን በአዕምሮአችን ውሳኔ አሳልፈን
ስለልብስ መጨነቅ እርግፍ አርገን ትተን
ገቢያችንን ሁሉ ለምግብ እያዋልን
በለመድነው መንገድ ስንጋፈጥ ኑሮን
በቅርበት የሚያውቁን በአለባበሳችን ግራ የተጋቡት
ለምን ብላችሁ ነው የተቀደደ ልብስ የምታዝወትሩት
ከእብደት አይለይም እራቁትን መሄድ ሰልባጅ በሞላበት
በዚህ ድርጊታችሁ ልታፍሩ ይገባል
ያያችሁ ሰው ሁሉ ይታዘባችኋል
አሁንም ፈጥናችሁ ሰልባጅ ልብስ ገዝታችሁ
ልትለብሱ ይገባል በደንብ አጽድታችሁ
ወደፊትም ቢሆን ልታውቁ የሚገባው
በሰዎች እይታ የእናንተን ማንነት በደንብ የሚገልፀው
አይነተኛው መስፈርት አለባበሳችሁ መሆኑን ማመን ነው
ብለው ግልጽ የሆነ ምክር ለግሰውን
በቀጣዩ ጊዜ ምክራቸውን ሁሉ ተግባር ላይ አውለን
በጣም ተለውጠን ሊያዩን እንደሚሹ ደጋግመው ነግረውን
በስተመጨረሻም ልንሰነባበት እንደተዘጋጀን
በዚህ በምክራችን ቅር ከተሰኛችሁ ይቅርታ አደርጉልን
እናንተን ለመጉዳት ሆን ብለን አስበን
ያደረግነው ድርጊት እንዳልሆነ እመኑን
ብለው ሲጨርሱ እኛም ቀበል አርገን
በለገሱን ምክር እጅግ ደስ እንዳለን
ውለታ ለመክፈል እግዜር ያብቃን ብለን
ተሰናበትናቸው በጣም አመስግነን
ከዚያም ለብቻችን ውይይት ጀምረን
ብዙ ተከራክረን አውጥተን አውርደን
የተሳሳተ አቋም ይዘን እንደቆየን
አሁን ልንቀይረው ፈቃደኛ እንደሆንን
በአንድ ድምጽ ወስነን ወደ ተግባር ገባን
ከዚያ በኋላማ ምኑ ይነገራል
ጠቅላላ ውሏችን ሰልባጅ ተራ ሆኗል
ኮት እንዲሁም ሱሪ የሱፍ አይነቶችን
ሸሚዝ ከ ክራቫት አብሮ የሚሄዱትን
በአይነትና ከለር መርጠን እየገዛን
በሳምንት ሁለቴ ስንለብስ እየቀየርን
ተሸፋፈነና የቤታችን ችግር የውስጥ ገመናችን
ጭራሽ መስለን ታየን ኑሮ የተስማማን
ለሰዎች የምንተርፍ ከእራሳችን አልፈን
በአይን እንኳን ለማየት ድሮ የሚፀየፉን
ሰልባጅ ስለለበስን ሽር ጉድ ሲሉልን
ለእራሳችን ጭምር በጣም እስኪገርመን
በሄድንበት ሁሉ ልዩ ክብርና ሰላምታ ሲሰጡን
በሰው ልጅ ከንቱነት እጅግ በጣም አዘን
Leave a Reply