Tag: 10+

  • እንባ (ሐምሌ 2000)

    ሰው አገር ሰላም ነው ብሎ በሙሉ እምነት

    ያለምንም ሀሳብ በተቀመጠበት

    ጭራሽ ለምን እንደሁ በማያውቀው ምክንያት

    ሰዎች የእሱን ክፉ ውድቀት ሲመኙለት

    ያልሠራውን ሠራህ በማለት ሲከሱት

    ሆን ብለው ደጋግመው በነገር ሲወጉት

    ፋታ አሳጥተውት ሰላሙን ሲነሱት

    ምነው ባልተፈጠርኩ እስኪል ሲያበሳጩት

    ስቃዩን አብዝተው ተስፋ ሲያስቆርጡት

    በመሸነፍ ስሜት መላ ቅጥ ጠፍቶበት

    የዉሸት ሳቅ ይስቃል ሳያስበው ድንገት

    ከዚያም መለስ ብሎ ጊዜ ሳይወስድበት

    የገዛ ድርጊቱ በጣም አስገርሞት

    ለካስ እንደዚህ ነው ወዶ አይስቁም ማለት

    አንጀት እያረረ ፈገግታ ማሳየት

    በማለት በልቡ እራሱን ታዝቦት

    ምንም ጊዜ ሳይወስድ በመጽናናት ስሜት

    ውስጣዊ ስሜቱን ሰዎች ካወቁበት

    ደካማ ነው ብለው እንዳይታዘቡት

    ወይም የማይወዱት ሊያዩት የማይፈቅዱት

    ሁኔታው አይተው ጮቤ እንዳይረግጡበት

    ብሶቱን አፍኖ እምቅ አርጎ ይዞት

    ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት

    ፍጹም ደስተኛ መስሎ ለመታየት

    ሳቅና ፈገግታ ፊቱን አፍክተውት

    እራሱን አታሎ ሌሎችን ሲያሳስት

    እንዲያው በአጠቃላይ ያለምንም ሀፍረት

    ያልሆነውን ሆኖ ሲቀርብ እሌሎች ፊት

    በጣም ያሳዝናል የዚህ አይነት ፍጥረት

    ፍጹም ወሰን የለሽ ይሉኝታ ቢስነት

    ሌላ ጊዜ ደግሞ ስናየው በቅርበት

    የሆነውን ሁሉ በጭራሽ ረስቶት

    ስሜት የሚነካ ወይ አሳዛኝ ክስተት

    ምንም ሳያስበው ድንገት ሲደርስበት

    በድንጋጤ ሀይል ማስመሰሉን ትቶት

    እንባውን መቋጠር በፍጹም ተስኖት

    ገንፍሎ ጉንጩ ላይ ሲፈስስ እንደ ጅረት

    በውስጡ ያለውን እውነተኛ ስሜት

    ሀዘኑን ፈንቅሎ ስለሚያወጣለት

    እርካታ ያገኛል የመንፈስ ነፃነት

  • እናት (መጋቢት 2000)

    የትውልድ መሠረት

    የፍቅር የውበት የደስተኛነት

    የተስፋ የብርታት የአርቆ አሳቢነት

    የሰላም የትግዕስት የሆደ ሰፊነት

    የንፁህ ልቦና የይቅር ባይነት

    ሰዎችን የማክበር ፈጣሪን የመፍራት

    ግራ ቀኝ የማየት ፍፁም ጠንቃቃነት

    የጥሩ ስብዕና በቃል የመገኘት

    የእኔ አለሁ ባይነት ቁም ነገረኛነት

    የመልካም ባህርይ የጥሩ ዳኝነት

    ያለማወላወል ውሳኔ ሰጪነት

    የህይወት ፈር ቀዳጅ መልካም መምህርነት

    ጊዜ የማይሽረው የልብ ወዳጅነት

    የመስዕዋትነት ቀድሞ የመገኘት

    የደግነት የእምነት የፍፁም ቅንነት

    የማስተዋልና እንዲሁም የፅናት

    መተኪያ የሌላት ጥሩ ምሳሌ ናት

  • ሁዳዴ (መጋቢት 2000)

    ሁዳዴን የማይፆም ፈጣሪን አይፈራም

    በጊዚያዊ እርካታ እየተደለለ አርቆ አያስብም

    ይጠቅመኛል ብሎ የሚገምተውን ምንም ይሁን ምንም

    ከማድረግ ፈጽሞ ወደ ኋላ አይልም

    አለማዊው ኑሮው በጣም ቢያረካውም

    መኖር ስለማይችል የሰው ልጅ ዝንተ አለም

    ምድራዊ ህይወቱ አንድ ቀን ሲፈፀም

    አላውቀውም ባለው በላይኛው አለም

    የዘለአለም ደስታ ሊኖረው አይችልም

    በደንብ ካስተዋልነው ይባስ ብሎ እንዲያውም

    ከሚገባው ቅጣት የሚያድነው የለም

    እያየ እየሰማ ይወርዳታል ገሀነም

    እያሉ ሲነግሩኝ ሁዳዴን የማልፆም መሆኔን የሰሙት

    ዘመድ ወዳጆቼ እንዲሁም ሌሎቹ የሚያውቁኝ በቅርበት

    በወጣትነቴ በዚያ በአፍላ ህይወት

    ይህን ማስፈራሪያ ሀሳቤን ሊያስቀይር ይችላል በማለት

    ምንም ባዩኝ ቁጥር ሆን ብለው ቢያነሱት

    እንኳን ሊፈጥርብኝ uንቀትና ፍርሀት

    አይሰጠኝም ነበር ምንም አይነት ስሜት

    ነገር ግን በሂደት ህይወቴን ስቃኘው

    ጊዜ ጊዜን ወልዶ አመታት ተቆጥረው

    በእድሜዬ ገፍቼ ተuኖኝ እርጅናው

    እልፈተ ህይወቴ መቼ ይሆን ጊዜው

    እያልኩ ስጠባበቅ ሁሉን ነገር ትቼው

    ከእለታት አንድ ቀን በሀሳብ ተውጨ

    በበርካታ አመታት ወደ ኋላ ሩጨ

    የወጣትነቴን ህይወት ስመረምር

    በድንገት ትዝ አለኝ የሁዳዴው ነገር

    ምንም ሞት አፋፍ ላይ እንዳለሁ ባውቀውም

    ምግብ ስለበላሁ በየሁዳዴው ፆም

    ለዘለአለም ሞት ፍርድ አለያም ለገሀነም

    ያበቃኛል ብዬ በፍፁም አላምንም

    ስጋ እንቁላል ቅቤ እንዲሁም አይብ መብላት

    እርጎ ወተትና መኪያቶ መጠጣት

    ሲኦል ውስጥ ካስገባ ሆኖ ከባድ ሀጢያት

    ወይም ፆምን መፆም ያለምንም ጉድለት

    ጠቀሜታ ካለው ገነት ውሰጥ ለመግባት

    ያኔ በልጅነት በጣም ስቆራመድ በአስከፊ ድህነት

    በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ጠግቤ ለመብላት

    በምቸገርበት ወይም ባዶ ሆዴን ፆሜን በማድርበት

    የዘወትር ኑሮዬም ፆም በነበረበት

    በዚያ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆነ ወቅት

    የምግብ ዘር ሳላይ ያለፉትን ቀናት

    ልቆጥራቸው ብችል ያለምንም ስህተት

    ሁሉንም ደምሬ የማገኘው ውጠት

    ተወልጄ እስክሞት ወለም ዘለም ሳለል

    ሁዳዴን ፆም ብፆም ምንም ሳላጓድል

    ህይወቴን በሙሉ ሁዳዴን ከፆምኩት

    በብዙ እጅ ይበልጣል በርሀብ ያሳለፍኩት

    እንግዲህ ይህ ሁሉ ከተቆጠረልኝ

    ቀጥታ ገነት ውስጥ ወስዶ እንደሚያስገባኝ

    ቅንጣት ያህል እንካ*ን ጥርጣሬም የለኝ

  • ለውጥ (መጋቢት 2000)

    የምናውቀውና አብሮን የኖረውን

    ኋላ ቀር አሠራር መለወጥ ተስኖን

    የተንዛዛ መንገድ ይዘን እየተጓዝን

    ህዝብን ማገልገል ነው ሥራችን እያልን

    ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ሲኖርብን

    መወሰን ስንችል እሺ ነገ እያልን

    በማያልቅ ቀጠሮ ሰው እያመላለስን

    በኢሰብአዊነት ባለጉዳዮችን እናንገላታለን

    ከዚያም አልፎ ተርፎ ገንዘብና ጊዜን እናባክናለን

    ለማስመሰል ብቻ ስለ ለውጥ ማውራት

    ነገር ግን በተግባር ምንም ያለመሥራት

    አለአዋቂነት ነው በጣም ትልቅ ስህተት

    ጎታች የሆነና ችግር የበዛበት

    ህግና መመሪያን ወይ የሥራን ሂደት

    ስንለምደውና ስናየው በሂደት

    ሊተካ የማይችል እንከን የሌለበት

    ጉድለቶች ለማየት

  • ወግ ፣ልማድ፣ እምነት እና ባህል (ታህሳስ 2000)

    ወግ ልማድና እምነት

    ከሰው ልጅ ህይወት ጋር የሚዛመዱበት

    በቃላት ለመግለጽ እጅግ የሚያዳግት

    በ ጣም የጠበቀ አላቸው ቁርኝት

    በጊዜ ሂደት ውስጥ አስተውለን ካየን

    የእለት ከእለት ኑሮ እንቅሰቃሴያችን

    እንዲያው በአጠቃላይ የእኛ የምንለው ሁሉም ታሪካችን

    ወግ ልማድና እምነት የተንሰራፉበት

    የአኗኗር ነፀብራቅ ጎልቶ የሚታይበት

    በጥቅሉ ባህል ብለው የሚጠሩት

    የእኛ መገለጫ ይህ ነው ትልቁ እሴት

  • ማንነት (መጋቢት 2000)

    የሰው ማንነቱ ዋናው መገለጫው

    ቃሉን ማክበሩና ታማኝነቱ ነው

    የሰውን ባህርይ ስንመረምረው

    ጠቅለል ባለ መንገድ ለሁለት ከፍለነው

    ማየት እንችላለን እንደሚከተለው

    በአንደኛው ወገን ውስጥ የምንመድበው

    ይሉኝታ የማያውቅ ለሰው ግድ የሌለው

    በአቋሙ የማይፀና ጥቅም የሚገዛው

    እንደእየ አጋጣ ሚው እንደእየ ሁኔታው

    መርሁን ሲቀይር ምንም የማይመስለው

    ፍጹም ሀፍረተቢስ ራዕይ የሌለው

    ከሌሎች ሰዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር

    ወይም ተቀራርቦ ተሳስቦ አብሮ መኖር

    በጣም እያስፈራው ሁሌ የሚሸበር

    በዚህ የተነሳ ከራሱ በስተቀር

    የሚያምነው ሰው አጥቶ ብቻውን የሚኖር

    እንዲያው በጥቅሉ ግለኝነት ስሜት የተፀናወተው

    ከእኔ በቀር ሌላ ቋንቋ የማይገባው

    ጥቅም ያሳበደው ሆኖ ስናገኘው

    ሁለተኛው ወገን ውስጥ የሚመደበው

    በጣም ጠንካራና ጊዜ የማይቀይረው

    የህይወት መመሪያ የፀና አቋም ያለው

    ቃሉን የማያጥፍ ክፉ የማይወጣው

    ወሬና አሉባልታ ፈጽሞ የማይፈታው

    መልካም ሀሳብና ጥሩ ዕራይ ያለው

    የሌሎች መቸገር እረፍት የሚነሳው

    ለአመነበት ነገር እውነት ለመሰለው

    ቆርጦ የሚታገል እስከ መጨረሻው

    አምኖ ያደረገው ወይም የወሰነው

    በእራሱም ላይ ጭምር ሊያደርስ የሚችለው

    ችግር ወይም ጉዳት ምንም የማይመስለው

    የእውነት ማንነቱ ጠቅላላ ስብዕናው

    በመስፈርቶች ሁሉ እንከን የማይወጣው

    ሰዎችን ማስደሰት ከልብ የሚያረካው

    ያለውን ለሌለው ከፍሎ የሚሰጥነው

  • ም ክ ር (መጋቢት 2000)

    ችግር ወይ መከራ ሰዎች ደርሶባቸው

    የዚያ መጥፎ ዜና መርዶ ተነግሯቸው

    ከመደንገጥ አልፈው እጅግ ተስፋ ቆርጠው

    በጣም በአጭር ጊዜ ፍጹም ሌላ መስለው

    የአካል እና መንፈስ ጉዳት አድክሟቸው

    የሚያያቸው ሁሉ እያዘነላቸው

    በቅርብ የሚያውቃቸው ሁሉም በየፊናው

    ይጠቅማል ያለውን ምክር ሲሰጣቸው

    የቱን ተቀብለው የትኛውን ትተው

    ቢሄዱ እንደሚሻል መምረጥ ሲያቅታቸው

    ያሉበት ሁኔታ የበለጠ አስከፊ ሆኖ እየታያቸው

    ዙሪያው ገደል ሆኖ መፍትሄው ጠፍቶባቸው

    ይይዝ ይጨብጡት አልታይ ሲላቸው

    የምክሩን ይዘት ሲያስቡት መላልሰው

    ምንም ሁሉም ጥሩ መስሎ ቢታያቸው

    ከዚህ ከጠቅላላው ጥቂት ብቻ መርጠው

    መፈጸም ቢያስቡ እንደማይችሉ አውቀው

    ምንም እንኳን ሰዎች ምክር ሲሰጧቸው

    ያጋጠማቸውን ችግር አሸንፈው

    ጊዜ ሳያጠፉ በቶሎ ተጽናንተው

    ኑሮአቸውን ከቀውስ ለማዳን አስበው

    በቅንነት መንፈስ ክልብ ተቆርቁረው

    የሚያደርጉት ነገር መሆኑን ተረድተው

    ፈታኝ በሆነው ወቅት ሰው ሲያስፈልጋቸው

    ከጎናቸው ቆመው አይዛ*ችሁ ላላ*ቸው

    ልባዊ ምስጋና ለሁሉም አቅርበው

    ጥሩ የሚመኝና የሚያስብላቸው

    ብዙ ሰው መኖሩን በመረዳታቸው

    በመንፈስ ታድሰው በተስፋ ተሞልተው

    ለአጭር ጊዜም ቢሆን በጣም ተደስተው

    ከዚያም እንደገና እንደባነነ ሰው

    ስለሰሙት ምክር ሲያስቡ መልሰው

    እንደ አዲስ አይተውት ጭራሽ በመገረም

    በተግባር የማይውል ምንም የማይጠቅም

    የምክር ጋጋታ ውጤት አይኖረውም

    ስለዚህ በከንቱ መድከም አይገባም

    የሚል መደምደሚያ ውሳኔ ላይ ደርሰው

    ምክርን አስመልክቶ ምን እንደታያቸው

    አሰቀምጠውታል እንዲህ ጠቅለል አርገው

    ምክር ተቀባዩን ግራ ቢያጋባውም

    ለሰጭው ቀላል ነው ምንም እይመስለውም

  • ሣቅ (መስከረም 2000)

    የደላውስ ይሳቅ ምኞቱ ተሳክቷል

    ነገር ግን የከፋው ሲስቅ ምን ይባላል)

    ቆሽቱ በጣም አሮ ስቃዩ በዝቶበት

    ገንፍሎ እንዳይወጣ ብሶቱን አፍኖት

    ዙሪያው ገደል ሆኖ መኖር አስጠልቶት

    ይይዝ ይጨብጠው መላ ቅጥ ጠፍቶበት

    እንዲያው በአጠቃላይ መከራና ስቃይ ተብትበው ይዘውት

    ተስፋ የቆረጠ ሰው ሲስቅ ብታዩት

    በጥርሱ ሊገልጽ ያሰበውን መልዕክት

    ውስጣ ዊ ስሜቱን ምንም ሳትረዱት

    ይህን ሰው ሳቀ ነው እናንተ የምትሉት)

    ሳቅንና ደስታን አንድ አርገን በማየት

    አስበውም ይሁን አልያም በድንገት

    ሰዎች ፈገግ ሲሉ ጥርሳቸውን አይተን

    ደስተኞች ናቸው ብለን ከደመደምን

    ሁል ግዜ ይህ ግምት እውነት ስለማይሆን

    የማይቀር ሀቅ ነው ስህተት መስራታችን

    ለዚህም ይመስላል ከልምድ በመነሳት

    አበው ጥርስ ባዕዳ ነው ሲሉ የሚሰሙት

  • ሆያ ሆዬ (ነሐሴ 1999)

    በዚያ ወጣትነት አፍላ ዘመናችን

    ከእኩዮቻችን ጋር አመት በአል ጠብቀን

    ብዙ ሳንደክም የገንዘብ ማግኛችን

    ሆያ ሆዬ ነበር ዋናው ጭፈራችን

    ስልቸት እስከሚለን መልሰን መላልሰን

    ስናንጎራጉረው ከቤት ቤት እየዞርን

    ያስደስተን ነበር የልጅ ድርጊታችን

    ከአመታት በኋላ በአዛውንት እድሜአችን

    ክፉም ደግም ጊዜ ሲፈራረቅ አይተን

    ምንም እንደማናውቅ ኑሮ እንዳልፈተነን

    የልጅነት ልማድ ተጠናውቶ ይዞን

    አሁንም እንደ ጥንት ልክ እንደ ዱሮአችን

    በነጋ በጠባ ሰው እስኪታዘበን

    ሆያ ሆዬ ብቻ ሆኗል ዘፈናችን

  • ሰውን ያለማወቅ (ህዳር 1990)

    በአስተሳሰቡና በጥሩ ባህርይው

    በፀባይ ቁመናው ጠቅላላ ስብዕናው

    ይስማማኛል ብለሽ ፍቅረኛሽ ያረግሽው

    አብረሽው ለመኖር ቃልሽን የሰጠሽው

    አልያም ፈቅደሽው በፍቅር አይን አይተሽው

    ፍቅረኛሽ እንዲሆን በሀሳብሽ መርጠሽው

    ስሜትሽን አውጥተሽ በግልጽ እንዳትነግሪው

    ባደግሽበት ባህል ዘመን ባሰቆጠረው

    ሴት ልጅ ወንድን ቀድማ ወደድኩህ ጸለችው

    ይህች ሰው አብዳ ነው ይህን ያረገችው

    ወይም ሀፍረተ ቢስ ስድ አደግ ብትሆን ነው

    ብለው እንደሚያሙሽ ጠንቅቀሽ አውቀሽው

    ከእሱ እስከሚመጣ የፍቅር ጥያቄው

    በተስፋ ተሞልተሽ የምትጠብቂው

    ከልብ የምትወጅው የእኔ የምትይው

    ቀልብሽን የሳበ የምታፈቅሪው ሰው

    ሊኖር እንደሚችል በሀሳቤ ሳልቃኘው

    እንደአሁኑ ገና ቀርቤ ሳላውቅሽ

    ክብርሽን መጠበቅ ስሜት የማይሰጥሽ

    ፍቅር የማይዝሽE ጥቅም የሚገዛሽ

    የተለየሽ ፍጡር አድርጌ ወስጀሽ

    እኔም እንደሌሎች መጀመሪያ ሳይሽ

    በቁንጅናዋ ነው ለዚህ የበቃችው

    ብዬ ደጋግሜ በሀሜት ቢላዋ እንዳልቦጫጨኩሽ

    ቀስ በቀስ በሂደት በደንብ ሳስተውልሽ

    መልጸም ፀባይና ሥራ አፍቃሪነትሽ

    ቅን አስተሳሰብሽ ሰው አክባሪነትሽ

    ከሰዎች ጋር ቶሎ መግባባት መቻልሽ

    በባህሪሽ ትሁት አስተዋይ መሆንሽ

    አስገድደውኛል በሌላ አይን እንዳይሽ

    መርህ ያለሽና በእምነትሽ የፀናሽ

    እንከን የማይወጣሽ ትልቅ ሰው እንደሆንሽ

    መገንዘብ ስለቻልኩ ቀረብ ብዬ ሳውቅሽ

    ለአንች የነበረኝ መጥፎ አመለካከት

    ተክለ ቁመናና አለባበስሽን ከሩቁ በማየት

    በእራሴ አዕምሮ ውሰጥ ቸኩዬ የሳልኩት

    የተሳሳተና ግምት የበዛበት

    ማንነትሽን ፍጹም የማያመለክት

    መሆኑን ጠንቅቄ ሰለተረዳሁት

    ይቅርታ እልሻለሁ ለአጠፋሁት ጥፋት

    ቃልም እገባለሁ ከልብ በመፀፀት

    አይለምደኝም ብዬ የዚህ አይነት ድርጊት

    ሰውን በደንብ ሳላውቅ ሰለዚያ ሰው ማውራት

    ወይም ያለስሙ ሌላ አዲስ ሰም መስጠት