ሰውን ያለማወቅ (ህዳር 1990)

በአስተሳሰቡና በጥሩ ባህርይው

በፀባይ ቁመናው ጠቅላላ ስብዕናው

ይስማማኛል ብለሽ ፍቅረኛሽ ያረግሽው

አብረሽው ለመኖር ቃልሽን የሰጠሽው

አልያም ፈቅደሽው በፍቅር አይን አይተሽው

ፍቅረኛሽ እንዲሆን በሀሳብሽ መርጠሽው

ስሜትሽን አውጥተሽ በግልጽ እንዳትነግሪው

ባደግሽበት ባህል ዘመን ባሰቆጠረው

ሴት ልጅ ወንድን ቀድማ ወደድኩህ ጸለችው

ይህች ሰው አብዳ ነው ይህን ያረገችው

ወይም ሀፍረተ ቢስ ስድ አደግ ብትሆን ነው

ብለው እንደሚያሙሽ ጠንቅቀሽ አውቀሽው

ከእሱ እስከሚመጣ የፍቅር ጥያቄው

በተስፋ ተሞልተሽ የምትጠብቂው

ከልብ የምትወጅው የእኔ የምትይው

ቀልብሽን የሳበ የምታፈቅሪው ሰው

ሊኖር እንደሚችል በሀሳቤ ሳልቃኘው

እንደአሁኑ ገና ቀርቤ ሳላውቅሽ

ክብርሽን መጠበቅ ስሜት የማይሰጥሽ

ፍቅር የማይዝሽE ጥቅም የሚገዛሽ

የተለየሽ ፍጡር አድርጌ ወስጀሽ

እኔም እንደሌሎች መጀመሪያ ሳይሽ

በቁንጅናዋ ነው ለዚህ የበቃችው

ብዬ ደጋግሜ በሀሜት ቢላዋ እንዳልቦጫጨኩሽ

ቀስ በቀስ በሂደት በደንብ ሳስተውልሽ

መልጸም ፀባይና ሥራ አፍቃሪነትሽ

ቅን አስተሳሰብሽ ሰው አክባሪነትሽ

ከሰዎች ጋር ቶሎ መግባባት መቻልሽ

በባህሪሽ ትሁት አስተዋይ መሆንሽ

አስገድደውኛል በሌላ አይን እንዳይሽ

መርህ ያለሽና በእምነትሽ የፀናሽ

እንከን የማይወጣሽ ትልቅ ሰው እንደሆንሽ

መገንዘብ ስለቻልኩ ቀረብ ብዬ ሳውቅሽ

ለአንች የነበረኝ መጥፎ አመለካከት

ተክለ ቁመናና አለባበስሽን ከሩቁ በማየት

በእራሴ አዕምሮ ውሰጥ ቸኩዬ የሳልኩት

የተሳሳተና ግምት የበዛበት

ማንነትሽን ፍጹም የማያመለክት

መሆኑን ጠንቅቄ ሰለተረዳሁት

ይቅርታ እልሻለሁ ለአጠፋሁት ጥፋት

ቃልም እገባለሁ ከልብ በመፀፀት

አይለምደኝም ብዬ የዚህ አይነት ድርጊት

ሰውን በደንብ ሳላውቅ ሰለዚያ ሰው ማውራት

ወይም ያለስሙ ሌላ አዲስ ሰም መስጠት

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *