ሁዳዴ (መጋቢት 2000)

ሁዳዴን የማይፆም ፈጣሪን አይፈራም

በጊዚያዊ እርካታ እየተደለለ አርቆ አያስብም

ይጠቅመኛል ብሎ የሚገምተውን ምንም ይሁን ምንም

ከማድረግ ፈጽሞ ወደ ኋላ አይልም

አለማዊው ኑሮው በጣም ቢያረካውም

መኖር ስለማይችል የሰው ልጅ ዝንተ አለም

ምድራዊ ህይወቱ አንድ ቀን ሲፈፀም

አላውቀውም ባለው በላይኛው አለም

የዘለአለም ደስታ ሊኖረው አይችልም

በደንብ ካስተዋልነው ይባስ ብሎ እንዲያውም

ከሚገባው ቅጣት የሚያድነው የለም

እያየ እየሰማ ይወርዳታል ገሀነም

እያሉ ሲነግሩኝ ሁዳዴን የማልፆም መሆኔን የሰሙት

ዘመድ ወዳጆቼ እንዲሁም ሌሎቹ የሚያውቁኝ በቅርበት

በወጣትነቴ በዚያ በአፍላ ህይወት

ይህን ማስፈራሪያ ሀሳቤን ሊያስቀይር ይችላል በማለት

ምንም ባዩኝ ቁጥር ሆን ብለው ቢያነሱት

እንኳን ሊፈጥርብኝ uንቀትና ፍርሀት

አይሰጠኝም ነበር ምንም አይነት ስሜት

ነገር ግን በሂደት ህይወቴን ስቃኘው

ጊዜ ጊዜን ወልዶ አመታት ተቆጥረው

በእድሜዬ ገፍቼ ተuኖኝ እርጅናው

እልፈተ ህይወቴ መቼ ይሆን ጊዜው

እያልኩ ስጠባበቅ ሁሉን ነገር ትቼው

ከእለታት አንድ ቀን በሀሳብ ተውጨ

በበርካታ አመታት ወደ ኋላ ሩጨ

የወጣትነቴን ህይወት ስመረምር

በድንገት ትዝ አለኝ የሁዳዴው ነገር

ምንም ሞት አፋፍ ላይ እንዳለሁ ባውቀውም

ምግብ ስለበላሁ በየሁዳዴው ፆም

ለዘለአለም ሞት ፍርድ አለያም ለገሀነም

ያበቃኛል ብዬ በፍፁም አላምንም

ስጋ እንቁላል ቅቤ እንዲሁም አይብ መብላት

እርጎ ወተትና መኪያቶ መጠጣት

ሲኦል ውስጥ ካስገባ ሆኖ ከባድ ሀጢያት

ወይም ፆምን መፆም ያለምንም ጉድለት

ጠቀሜታ ካለው ገነት ውሰጥ ለመግባት

ያኔ በልጅነት በጣም ስቆራመድ በአስከፊ ድህነት

በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ጠግቤ ለመብላት

በምቸገርበት ወይም ባዶ ሆዴን ፆሜን በማድርበት

የዘወትር ኑሮዬም ፆም በነበረበት

በዚያ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆነ ወቅት

የምግብ ዘር ሳላይ ያለፉትን ቀናት

ልቆጥራቸው ብችል ያለምንም ስህተት

ሁሉንም ደምሬ የማገኘው ውጠት

ተወልጄ እስክሞት ወለም ዘለም ሳለል

ሁዳዴን ፆም ብፆም ምንም ሳላጓድል

ህይወቴን በሙሉ ሁዳዴን ከፆምኩት

በብዙ እጅ ይበልጣል በርሀብ ያሳለፍኩት

እንግዲህ ይህ ሁሉ ከተቆጠረልኝ

ቀጥታ ገነት ውስጥ ወስዶ እንደሚያስገባኝ

ቅንጣት ያህል እንካ*ን ጥርጣሬም የለኝ

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *