በጥፋትም ሆነ ወይም ያለ ጥፋት
በሆነ አጋጣሚ ሰው ከገባ አስር ቤት
ማስረጃ ተይዞ ምስክር ቀርቦበት
ጥፋቱ ተገልፆ ሳይፈረድበት
በቁጥጥር ውሎ ስለሆነ እስረኛ
ብዙ ሰው ያየዋል እንደ ወንጀለኛ
ወዳጅ ጓደኞቹ በጣም የሚቀርቡት
ወደ አስር ቤት ሄደው አንዴም ሳይጠይቁት
ስለሚያውቁት ብቻ በፍርሀት ተውጠው
የእሱ ወንጀል አልፎ እንዳያስቀጣቸው
እሱን አናውቀውም ምንም የለም ቅርበት
ለፈፀመው ወንጀል ይገባዋል ቅጣት
ብለው ያለማፈር ምንም ሳያጣሩ ያጠፋውን ጥፋት
በወንጀለኛነት ቀድመው ሲፈርዱበት
ያኔ ይጀምራል ዙሪያውን መመልከት
ያለፈውን ጊዜ በጥሞና ማየት
ለመረዳት መሻት ትክክለኛውን የሰዎች ማንነት
ምን እንደሚመስል የውስጥ ስሜታቸው
ደብቀው የያዙት የእውነት ባህሪያቸው
አጋጣሚ ሲገኝ ገሃድ የሚወጣው
ይህንን ለማወቅ ባለው ጥልቅ ስሜት
የሚያውቀውን ሁሉ መመዘን ይይዛል ባስቀመጠው መስፈርት
ማን ጊዜ ለውጦት ፊት እንዳዞረበት
ወይም ሳይቀየር ማን እንደቆመ አብሮት
ማን ምን እንደሆነ ጠንቅቆ መረዳት
ብዙ ወዳጆቹ ድሮ የሚቀርባቸው
ተለዋዋጭ አቋም ይዘው ሲያገኛቸው
ትውት ሲያደርጉት ልክ እንደማያውቁት
ጎልቶ ይታየዋል የሰው ልጅ ከንቱነት
ከቶ እንደማይቻል እምነት ሊጣልበት
እንደማይገባ እገሌ አለኝ ማለት
በደንብ ሳያጤኑ የሰውን ማንነት