ዝምታ ወርቅ ነው (መስከረም 1993)

በምኔ ልናገር አፌ ተሸብቦ

በፍርሃት ተውጬ ወኔዬ ተሰልቦ

በእኔነቴ አምኜ እራሴን እንዳልችል

የሚሉኝን ሁሉ በሙሉ እንድቀበል

የሰውነቴ አርማ የእኔን መገለጫ

የግል አእምሮየን የሃሳቤን ማመንጫ

የራሳቸው አድርገው እንዳሻቸው ሊያዙት

ፍፁም እንዳይኖረኝ የማሰብ ነፃነት

እንዳላመዛዝን ህሊናዬን ስቼ

እነሱን እንዳመልክ ሁሉን ረስቼ

ተስፋዬ እንዲጨልም በሀሳብ ሎሌነት

አንደበቴ ታስሮ የሞት ሞት እንድሞት

ስሜቴ እንዲኮላሽ ፍፁም ፈሪ እንድህን

በየደረስኩበት የምናገረውን

ይከታተላሉ ከአፌ የሚወጣውን

አንድ ነገር ብዬ ከገለፅኩ ሃሳቤን

ይጨምሩበታል እኔ ያላልኩትን

አለ የተባልኩት በወሬ ቀበኞች አምሮ ተከሽኖ

ጣፍጦ ስለሚቀርብ ተባዝቶ ተጋኖ

ብዙ ጊዜ ሳይቆይ ቶሎ ያራቡታል

እየሰነጠቁ ትርጉም ይሰጡታል

እኔን ለመወንጀል ይጠቀሙበታል

ጆሮውን ቀስሮ የሚያሳድድ ነገር

ምላሱን አሹሎ ተናግሮ የሚያናግር

ወሬ የሚለቅም የሰው ወፍ ሲመጣ

ጥርጣሬ ነግሶ መተማመን ታጣ

ብሶቴን አውጥቼ እንዳልናገረው

የማን ምንነቱን ስላልቻልኩ ላውቀው

መመሪያዬ ሆኗል ዝምታ ወርቅ ነው

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *