ሰውና ኑሮው (ነሐሴ 1997)

ረቂቅ ሥራውን አምላክ ያሳየበት

ሰውን ከእራሱ ጋር አመሳስሎ ፈጥሮት

ፍጡራን በሙሉ ለእሱ እንዲታዘዙት

በኑሮው ሂደት ውስጥ ብዙ ሁኔታዎች ሲፈራረቁበት

መራራት መፀፀት መታገስ መደሰት

መጨከን መከፋት ማዘን መበሳጨት

ሌሎች ልዩ ልዩ የሆኑ ስሜቶች እንዲፈጠሩበት

ጥሩውን ከመጥፎ ለይቶ እንዲያውቅበት

ከሁሉም የላቀ አዕምሮ እንዲኖረው

የሰውን ልጅ ልዩ አርጎ መፍጠሩ ነው

ከወላጆቹ አብራክ አምላክ መርጦ ፈጥሮት

እድገቱን ሲጨርስ አልፎ ከጽንስነት

የእናቱን መሀፀን ለቆ የሚወጣበት

አለምን ፊት ለፊት የሚጋፈጥበት

ጊዜው መዳረሱን የሚገልጽ ምልክት

መታየት ሲጀምር ወዲያው ከመቅጽበት

ያን ጊዚያዊ ቤቱን ፈጥኖ ተሰናብቶት

ጉዞውን ጀምሮ ወደ ውጭ ለመውጣት

ይችን አለም ገና ብቅ ብሎ ሲያያት

ሁሉም ሁኔታዎች ከተመቻቹበት

ተሰናብቶ ትቶት ከመጣው ቤቱ ጋር እያነፃፀራት

በፍርሀት ተውጦ መመለስ ሲያቅተው ወደነበረበት

ያለውድ በግድ መውጣት እንዳለበት ግልጽ ሲሆንለት

ብዙ ፈተናዎች እንደሚጠብቁት አስቀድሞ ታይቶት

ምርር ብሎ አልቅሶ አለም መጣሁልሽ ተቀበይኝ ሲላት

እሷም ፈጠን ብላ መልስ ስትመልስለት

ምክር ወይም ቁጣ ብሎ ለመለየት በጣም የሚያዳግት

በአንፃሩ ግን ደግሞ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት የሞላበት

መልዕክት እንደያዘ ይቻላል መረዳት

እማራጭ የለህም ዝም በልና ውጣ

ምኑንም ሳታየው እንዲሁ አትንጣጣ

ወደፊት ሲገባህ እንዴት እንደሚከብድ ኑሮ የሚባል ጣጣ

ድጸምህ ልፋትህ ምንም ዋጋ ሲያጣ

ያኔ ምንም አይደል እርምህን ብታወጣ

ስለዚህ ዝም በል አሁን ማልቀስ ይብቃህ

ጊዜ ሳታጠፋ ቶሎ ፈጠን ብለህ

የማይቀር ነውና ከአዲሱ ኑሮህ ጋር መላመድ አለብህ

ምክሬን ከሰማኸኝ እኔ የምነግርህ

ፈተናና ችግር ፈጽሞ እንዳይፈታህ

ትግፅስትና ተስፋን አድርገህ መመሪያህ

ጠንክረህ በርትተህ መሥራት ነው ያለብህ

ይኸ ነው ባጭሩ ማድረግ የሚገባህ

የሚል ጠለቅ ያለ ምክር የበዛበት

ሞቅ ያለ አቀባበል ስትዘረጋለት

ይህ አዲስ ሁኔታ ቀልቡን በጣም ስቦት

ምኑንም ሳላውቀው የለብኝም መፍራት

ጥሩ ነገሮች ነው እስከ አሁን ያየሁት

ስለዚህ ከአሁኑ ተስፋዬን አልቆርጥም ስለመጪው ህይወት

ጭራሽ መጥፎ ብቻ አይሆንም በእኔ እምነት

ያም ሆኖ አልቸኩልም እንዲህ ነው ለማለት

እጠባበቃለሁ ሁሉንም በትግዕስት

ብሎ ይጋፈጠዋል ያን አዲሱን ህይወት

ጊዜ የሚያመጣውን በሂደት ለማየት

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *