ያንገት ጠቀሜታ ያልገባን ብዙ ነን
የማንመለከት ግራ ቀኝ እያልን
ከፊት ለፊት ብቻ የምናይ አፍጥጠን
ወደሗላ ዞረን ጭራሽ የማንቃኝ
በፈጠርነው አለም በህልም የምንዋኝ
ፍፁም የምንረሳ ማንነታችንን
ጊዜያዊ ደስታና ጥቅም የሚገዙን
መርህ ያደረግነው ሆድ አምላክነቱን
አንገት መፈጠሩ አዙሮ ለማየት መሆኑን እረስተን
በደመነፍስ ያለን ተነድተን በስሜት
ጥሩውን ከመጥፎ ያቃተን መለየት
በጣም ብዙዎች ነን አርቀን የማናይ
ስሜት የማይሰጠን የሌላው ሰው ጉዳይ
ሁሌ የሚመስለን በኛ የማይደርሱ መከራና ስቃይ
ለኛ የሚል ቋንቋ ፍፁም የማይገባን
አዕምሮአችን ዞሮ የማናመዛዝን
ማሰብ የተሳነን ሁሌ ለእኔ የምንል
የመኖር ትርጉሙን መረዳት ያቃተን
የራሳችን ጉዳይ ሁል ጊዜ ሌት ተቀን ፋታ የማይሰጠን
የምናብሰለስል በተንኮል ተሞልተን
ሌሎች ሲቸገሩ ፀጥታን የምንመርጥ ጆሮአችንን ደፍነን
በጣም ብዙዎች ነን ለኔ ከሚል ቃል ውጭ ሌላ የማይጥመን
በጥቅም ታውሮ ሁሌ መስገብገቡ
ለብቻ መኖሩ ለራስ እያሰቡ
ፍፁም ተለይቶ ከህብረተሰቡ
ስብዕናን መጸድ ነው ተፈጥሮን መጋፋት
ጭራሽ ያለማወቅ የሰውን ማንነት
በጣም መጠራጠር የአዕምሮውን ብስለት
ሰውን ማመሳሰል ከእንስሳት ጸራዊት
ግለኝነት በጣም የተወገዘ ነው በታሪክ በባህል
ይህን በማስመልከት በሃገራችን አለ አንድ ጥሩ ብሂል
ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል
ተብሎ የሚነገር ስለ ግለኝነት
በምሳሌነቱ ወደር የሌለለት
መስታወት የሚሆን ለሚጠቀምበት
የሰው ልጅ በህብረት መኖር እንዳለበት
ለሚገባው ሁሉ ሰጪ ጥሩ ትምርት
የምንኖርባት ይህች ምድራዊ አለም
የብድር መሆኗን መርሳት የለብንም
ለመቀበል መስጠት ለማጨድም መዝራት
እንደሚያስፈልጉ መታወቅ አለበት
ለእኔ በሚል ፈሊጥ የራስን በር ዘግቶ
በደንታ ቢስነት ሌላውን ረስቶ
መኖር ለራስ ብቻ የሚለው ተኩራርቶ
የሚያደርገው ሲያጣ ችግር ሲያግጠመው
ቀኑ ጨልሞበት ሲያጥርበት ማጣፊያው
መቅረብ ይጀምራል የማያውቀውን ሰው
ቅብጥብጥ ማለት ችግሩን ሊያዋየው
ቅልብጭ ያለ መፍትሄ በቶሎ እንዲሰጠው
ያደረገው ድርጊት ምስከር ሆኖበት
በችግሩ ጊዜ ሲያጣ የሚደርስለት
ማሰብ ይጀምራል ስለ እራሱ ህይወት
ላለፈው ድርጊቱ ከልብ መፀፀት
ማንነቱን ክዶ ሸፋፍኖ ስራውን
መረዳት ሲጀምር መኖር እንደማይችል ከእንግዲህ ብቻውን
ያኔ ይጀምራል አዙሮ መመልከት
ከሰው ጋር ለመኖር አዕምሮውን መክፈት
ጠልቆ መመራመር ስለ ሰው ማንነት
ግለኝነትንም አጥብቆ መዋጋት
Leave a Reply