ሠፈራ (ጥቅምት 1997)

የችጋር የጠኔ የሰፈራ ጣጣ

አሁንም እንደ አዲስ እንደገና መጣ

ድርቅ ርሃብን ወልዶ የሚበላ ጠፍቶ

ሰው ተስፋው ሲጨልም ወገን ደራሽ አጥቶ

በመሸነፍ ስሜት እጁን ለሞት ሰጥቶ

ቀስ በቀስ ሲደክም ርሃቡ ጠንቶበት

የወደፊት እጣው ሲደበዝዝበት

ህይወቱን የሚያድን መፍትሄ ሲቀርብለት

ምንም ሳይመዝነው ሳያየው በጥልቀት

ተቀበልኩት ይላል ትንሽ ለመሰንበት ባደረበት ጉጉት

ብቸኛው አማራጭ ለማትረፍ ህይወቱን

መሆኑን ሲረዳ ቶሎ ለቆ መሄድ ቀየውን መንደሩን

ከዚያም ሌላ ቦታ ሄዶ ራስን ማስፈር

በማያውቁት አገር አዲስ ኑሮን መኖር

ምን እንደሚሻለው ግራ በመጋባት

ከዚህ ልሂድ እና ህይውቴን ላትርፋት?

ወይስ ልቆይና እዚሁ አገር ልሙት
በማለት ደጋግሞ እራሱን ጠይቆ

ባማራጮች መጥበብ ከልብ ተጨንቆ

በሃሳብ ባህር ውስጥ ስጥም ብሎ ጠልቆ

አልታይህ ሲለው ምን እንደሚያዋጣው

ከእንቅልፉ እንደነቃ እንደባነነ ሰው

እየተወራጨ ተውጦ በፍርሃት

ክርክር ይይዛል ከራሱ ጋር ሙግት

ለመሄድ ብወስን መድረሻዬ የት ነው

ከዚህ መሻሉንስ እንዴት ነው የማውቀው

ስለዚህ ይቅርብኝ እዚህ እቆያለሁ

መሞት ጸለብኝም የማይቀር ነውና እዚሁ በፀጋ እቀበለዋለሁ

ብሎ ብዙ ሳይቆይ ለውጦ ሃሳቡን

አሁን ለምን ልሙት መሰንበት እየቻልኩ ማቆየት ህይወቴን

በቃ ቆርጫለሁ ልሂድ ሃገር ጥዬ

ከመሞት መሰንበት ይሻለኛል ብዬ

ይህ አዲስ ውሳኔው አላረጸህ ሲለው

ማሰብ ማሰላሰል ይጀምራል ወዲያው

ምን እንደሚመስል የወደፊት ኑሮው

በማያውቀው ሃገር ስለሚያጋጥመው

በዚህ አይነት መንገድ ሲቀይር አቋሙን

መልሶ መላልሶ ሲሽር ውሳኔውን

ከዚያም እንደገና ሲጠይቅ እራሱን

ባቋሙ ለመፅናት ማድረግ ያለበትን

ይህን ሁሉ አድርጎ ሲሳነው መወሰን

ከልብ የሚያምነውን ጋሻ መከታውን

ማማረር ይይዛል ሃያል ፈጣሪውን

በግልፅ ይነግረዋል ጠቅላላ ብሶቱን

ከቶ ለምንድነው እንዲህ መጨከንህ

ምነው እረሳኸን በዘዛብን ፈተነናህ

አንተም እንደ ሰው ልጅ አድልኦ ታውቃለህ

ወይስ እኛን ብቻ መከራና ስቃይ ይችላሉ ብለህ

የችግር አውድማ ልታደርገን አሰብህ?

በረሃብ ተሰቃይተን አማቀን እንዳንሞት

እኛን ለመታደግ ከችግር ለማውጣት

ከአቅምህ በላይ ሆኖ እንዳላስቸገረህ

ምስክር ነውና ተአምራዊ ሃይልህ

በረሃብ ስንረግፍ ታዛቢ መሆንህ

ፍፁም አልገባኝም ምንድነው ሚስጥርህ

ፍጣሪን ተጋፋህ ተዳፈርክ ባይሉኝ

ስላንተ ማንነት መረዳት አቃተኝ

ሁሉን እየቃኘህ እያየህ በእኩል አይን

ረሃብ ሲጨርሰው አምሳያ ፍጡርህን

ዝም ብለህ ታያለህ ብዬ ስለማላምን

እጠራጠራለሁ በእውነት መኖርህን

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *