ሰው ቃሉን ሲሰጠን መተማመኛውን
ሲያረጋግጥልን የሀሳብ ፅናቱን
ቃሌ ቃል ነውና አትጠራጠሩኝ
በቃሌ እቆማለሁ ስለዚህ እመኑኝ
በማለት ደጋግሞ አጥብቆ ሲነግረን
አንጠራጠርም እንደሚያከብር ቃሉን
አስገራሚው ነገር የሚያስተዛዝበው
ሰው የገባውን ቃል አፍርሶ ሲገኝ ነው
የተናገረውን ጭራሹን ለውጦ
ሌላ ሆኖ ሲገኝ እምነቱን አሟጦ
አይኑን በጨው ታጥቦ እንደ አዲስ ሲቀርበን
የገባልንን ቃል አላውቀውም ሲለን
ምን ትሉታላችሁ ይህን እምነተ ቢስ
ህሊናውን ሽጦ ያለውን የሚያፈርስ
ባስቀመጡት ቦታ የማይገኘውን
ለዜያዊ ጥቅም ሰልፍ የሚቆመውን
በአምሮው ለማሰብ ያልተፈጠረውን
በውሸት ባህር ውስጥ የሚዳክረውን
ቃሉን የማያከብር እምነት የሚያጎድል
እንስሳ ነው እንጅ አይችልም ሰው ሊባል
Leave a Reply