የርሀብተኞች ድምፅ (ሰኔ 1996)

እምዬ ተፈጥሮ ፊቷን አዙራብን

አዝመራችን ደርቆ አልቀው ከብቶቻችን

ቀያችን ተራቁቶ ተሟጦ ጓዳችን

የምንቀምሰው አጥተን የምግብ ዘር ናፍቆን

ሆዳችን ተጣብቆ ርሀቡ ጠንቶብን

በማዛጋት ብዛት ተላቆ ላንቃችን

ተስፋችን ጨልሞ ከሞት ጋር ተፋጠን

ዛሬን አልፈን ነገ የምንኖር ሳይመስለን

ዙሪያው ገደል ሆኖ መላው ሲጠፋብን

ፈጣሪም ሲመስለን እንደ ሰው የረሳን

ለችግር ለስቃይ አሳልፎ ሰጥቶን

የሰው ከብት ስንሆን በመኖር አባዜ

ሳር ቅጠል በመብላት ስናሳልፍ ጊዜ

ችግሩ ጠንቶብን መቋቋም ሲያቅተን

ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጭ ግብግብ ገጥመን

ወገኖቻችንን ሞት እየነጠቀን

ተራ እንጠብቃለን በሲቃ ተይዘን

ዛሬን ጸሳለፍናት የነገውን እሱ አንድዬ ያውቀወዋል

መቼም አይጨክንም ተዐምሩን ያሳያል

ፍጡሩን አይረሳም ምህረቱን ያወርዳል

መከራችሁ በዝቷል በቃችሁ ይለናል

በሚል አጉል ተስፋ በከንቱ ተሞልተን

የመኖር አባዜ ተጠናውቶ ይዞን

ሞት እንዳይደርስብን እንማፀናለን

ከዚህ ከኑሮአችን ነጥሎ እንዳይወስደን

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *