አማርኛ (ግንቦት 1996)

ምነው አማርኛ ጭራሹን ቅጥ አጣሽ

አንችነትሽ ጠፋ ከባዕድ ጋር ተዳቅለሽ

አንዱን ቃል ከአንዱ ላይ እንዳለ እየወሰድሽ

ሌላውን ከሌላ ቀላውጠሽ አምጥተሽ

በመቀየጥ ብዛት ሌላ መስለሽ ቀረብሽ

አምናለሁ አትረሽም እንችን እንደማውቅሽ

በጥሞና አድምጭኝ ጭንቀቴን ላዋይሽ

በአንች አፌን መፍታቴን

በልጅነቴ ወቅት ትምህርቴን መማሬን

በደንብ አውቅሻለሁ ብዬ መፎከሬን

የዱሮ ታሪክ ነው ተወው አታስታውሰው

የጥንቱን አታንሳ እያልሽኝ ነው እርሳው?

እባክሽ ንገሪኝ የውስጥ ስሜትሽን

በእውነት ወደድሽው የአሁን ማንነትሽን?

ገፎ የጣለውን ያን ድንቅ ውበትሽን

መልስ ስጪኝ እንጂ ዝምማ አትበይኝ

የአንች እንዲህ መቀየጥ እረፍት ሲያሳጣኝ

መልስሽ ይሆን እንዴ ጥፋት የለብኝም

መስዬ መኖሬ አያስጠይቀኝም

ልትወቅሰኝ አትችልም በአሁን ማንነቴ

ያስመሰግነኛል መትረፉ ህይወቴ

ወይስ ልትይ ይሆን ለእኔ አታስብልኝ

አውቀዋለሁና ምን እንደሚያዋጣኝ

እኔን ተወት አርገህ እራስህን መርምር

ትላንት ዛሬ አይደለም ብለህ ማሰብ ጀምር

ያኔ ትረዳለህ የእኔነቴን ሚስጥር

ግልጽ ሲሆንልህ ግዴታ እንደሆነ ጊዜን መስሎ መኖር

በእርግጥ እያልሽኝ ነው ሚስጥሬ አልገባህም?

ይህ ጠባቡ እይታህ የትም አያደርስም

ማን እንደተገኘ ባስቀመጡት ቦታ

በእኔ መለዋወጥ ተሰማህ ቅሬታ

ስለዚህ አዘጋጅ ለለውጥ እራስህን

ይጠቅምሀልና በደንብ ስማ ምክሬን

ወደ ኋላ እንዳትቀር ከሰው ተነጥለህ

ከጊዜ ጋር ተጓዝ ቶሎ ቀልጠፍ ብለህ

ይህ ከሆነ አቋምሽ የምትከተይው

አላስቸግርሽም ጥያቄዬን እርሽው

በቃ አልናገርም ሃሳብሽ ገብቶኛል

ስሜቴን አፍኜ ዝም ብል ይሻለኛል

ነገር አላበዛም በዚሁ አቆማለሁ

ምላሽሽ ከሆነ መስዬ እኖራለሁ

ጭራሽ እንዳትጠፊ እመኝልሻለሁ

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *