ሰዎችን ለመውቀስ ወይም ለማመስገን
ፍፁም አትቸኩል ተጠቀም ጊዜህን
የሰውን ማንነት የውስጥ ስሜÜቱን
ለማወቅ ከፈለክ ድብቅ ስብእናውን
በጊዜ ሚዛን ላይ አስቀምጠህ ለጸው
መከራና ችግር ሲደርስብህ እየው
በደስታህ ጊዜ ሁሉም ሲሰምርልህ
ምሎ ተገዝቶ የሚል አለሁልህ
ሊፈተን ይገባል ችግር ሲያጋጥምህ
የሰው ያለህ ስትል ደራሽ ወገን አጥተህ
ብቻህን ስትቆም ቀኑ ጨልሞብህ
ሰው በሚያስፈልግህ በዚህ በፈታኝ ወቅት
ከራስህ ጋር ሙግት በምትገጥምበት
ማስተዋል አለብህ የዚህን ሰው ድርጊት
አለሁልህ ብሎ ከጎንህ ይቆማል?
ወይስ ይሸሽሃል?
ልክ እንደማያውቅህ ጥሎህ ይሰወራል?
ይኸ ነው ሚዛኑ የሰው መገለጫው
ክፉውን ከደጉ ለይቶ የሚያሳየው
Leave a Reply