አብዛኛው እድሜዬን ኑሮን እየታገልኩ
ማሸነፍ ባልችልም ተስፋ ስላልቆረጥኩ
በደመ ነፍስ ብቻ እየተፍጨረጨርኩ
ብዙ መከራና ስቃይ ስለአሳለፍኩ
ኑሮዬን እንደ አዲስ ልጀምር ስለአሰብኩ
ቀደም ባለው ጊዜ አለሁ ባይ አጥቼ
የደረሰብኝን የሆንኩትን ሁሉ ወደ ኋላ ትቼ
በሰዎች ላይ ላልደርስ ምዬ ተገዝቼ
ስሜቴን አፍኜ አንገቴን ደፍቼ
ጠብና ትንኮሳን ከሩቅ እየሸሸሁ
ነገሮችን ሁሉ በጥሞና እያየሁ
በጣም ተጠንቅቄ ስመራ ህይወቴን
በደንብ ያልተረዱት ድርጊቴና ሀሳቤን
ሰዎችን የምንቅ ኩራት የወጠረኝ
አልያም አውቆ አበድ አድርገው ቆጥረውኝ
ምክንያት ፈልገው ስሜቴን ሲጎዱት
ትግዕስቴን ደጋግመው በጣም ሲፈትኑት
ወይም ስሜን አውቀው በከንቱ ሲያጠፉት
ለእኩይ ድርጊታቸው አፀፋ ከመስጠት
የፈለገው ይምጣ በሚል አይነት ስሜት
በንቀት እያየሁ ዝም ብዬ ሳልፋቸው
ክንፍ የሌለው እርግብ መብረር የተሳነው
አድርገው ቆጥረውኝ መሄጃ የሌለው
ተዉ ባይ በሌለበት እስኪያንገሸግሸኝ
በበደል ላይ በደል ሲደራርቡብኝ
ለማን አቤት ብዬ ሰላም እንደማገኝ
ወይስ ምን ብሠራ እንደሚራሩልኝ
አውጥቼና አውርጄ መፍትሔ ሲጠፋብኝ
እንዲህ ከምሰቃይ ምነው ባልፈጠርከኝ
ብዬ በማማረር ፈጣሪን ወቀስኩኝ
ከዚያም ብስጭቴ በረድ ሲልልኝ
እግዜርን መውቀሴ አውቆ እንደበደለኝ
ጥቅም እንደሌለው ስለተረዳሁኝ
ከሁሉም በላይ ግን ጥሎ የማይጥለኝ
ኃያሉ ፈጣሪ አብሮኝ አጠገቤ መኖሩ ተሰምቶኝ
ምንም ባስቀይመው ልጁ ስለሆንኩኝ
ይቅር እንደሚለኝ ሙሉ እምነት አድሮብኝ
ይህን መከራየን አንተው አቅልልኝ
በማለት መልሼ በጣም ተማፅኘው
ቀሪ ህይወቴንም እሱ እንዲባርከው
በተደጋጋሚ ሳልሰለች ለምኜው
በጣም ስረጋጋ ሁሉን ለእሱ ትቼው
የእኔ ሰላም ማግኜት ያላስደሰታቸው
ያደረጉት ሁሉ አልበቃ ብሏቸው
በህይወት መኖሬ ቁጭት ፈጥሮባቸው
ከምድር ገጽ ላይ እንድጠፋላቸው
እጅግ ሲጨነቁ ሲደክሙ ሳያቸው
የሰው ልጅ ጭካኔ ወሰን እንደሌለው
በህይወት ዘመኔ በእኔ የደረሰው
ትምህርት ሰጥቶኛል ሁል ግዜ የማረሳው
በዚህ የተነሳ በጥሞና ሳየው
የዚህ አይነት ኑሮ ውሸት የበዛበት
ክፋትና ተንኮል ስር የሰደዱበት
ሰው እርስ በእራሱ የሚጫረስበት
ትርጉም ስለሌለው ለሰው ልጆች ህይወት
እስከዘላለሙ ሀጢያት የሚባለው ከስሞ የሚጠፋበት
ያ ስምንተኛው ሺህ የአለማችን ህልፈት
እንዲሆን ፀለይኩኝ አሁን ከመቅፅበት
Leave a Reply