ማልቀስ እንደ ወንጀል (ነሐሴ 2000)

በስልሳዎቹና ሰባዎቹ አመታት

ልጃቸውን ገለው የመንግስት አካላት

ሀዘን ቁጭ ብላችሁ እንዳንመለከት

ወይም ስታለቅሱ አንፈልግም ማየት

እያሉ በድፍረት ለቅርብ ዘመዶች ለእናትና ለአባት

ሀይለ ቃል ያዘለ ማስጠንቀቂያ መስጠት

ከዚያም አልፎ ተርፎ ያለምንም ሀፍረት

የጥይቱን ዋጋ እንድትከፍሉ ማለት

በጽሁፍ የሌለ አንቀጽ ያልወጣለት

ነገር ግን ሰው ሁሉ አንድ ቀን በሂደት

እንደማይቀርለት አውቆ በተጠንቀቅ መጠበቅ ያለበት

ይግባኝ የሌለበት ፍርድ ሆኖ ነበር ለጥቂት አመታት

ያብራካቸው ክፋይ ወልደው ያሳደጉት

ውድ ልጃቸውን ያለፍርድ ገድለውት

አታልቅሱ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ መስጠት

አረመኔነት ነው ርህራሄ ማጣት

ሀዘንና ለቅሶን የከለከሉበት ትልቁ ምክንያት

የሌሎች ወላጆች ከዚህ ቀስምው ትምህርት

ልጆቻቸው ሁሉ እንዳይሰለፍ በተቃዋሚነት

እንዲያገለግል ነው በማስፈራሪያነት

በፍጹም ጭካኔ ማን አለብኝነት

ሆን ብሎ የሟቹን ወላጀች ለመጉዳት

የልጃቸውን ሞት ፈጽሞ እንዳይረሱት

ባስታወሱት ቁጥር እንዲሆንባቸው የዘለአለም ፀፀት

ፋታ እንዲያሳጣቸው ልክ እንደ እግር እሳት

የማድረግ እርምጃ ኢሰብአዊ ድርጊት

በታሪክ ያልታየ ተው ባይ የጠፋበት

ያለምንም ገደብ ህግ የሚጣስበት

መረን የለቀቀ ስርአተ አልበኝነት

ተንሰራፍቶ ነበር በሀገራችን ውስጥ በሁሉም ማዕዘናት

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *