የሰው ልጅ ስሜቱን የሚገልጽባቸው
ድርጊቶች ልዩና በጣም ብዙ ናቸው
ሀዘንን በለቅሶ ደስታን ደግሞ በሳቅ
ምንም ብዙ ጊዜ እንደሚገልጽ ብናውቅ
አልፎአልፎ ይታያል ፍጹም ሳይጠበቅ
እኒህ ስሜቶቹ ሲሉበት ድብልቅልቅ
አንዳንዴ በድንገት ምክንያቱን ሳናውቅ
እናገኘዋለን በደስታ ተሞልቶ በጣም ሲንሰቀሰቅ
ወይም ከልብ አዝኖ ከት ብሎ ሲስቅ
በደንብ አስተውለን በጥልቀት ካየነው
ደስታ የሀዘን ምንጭ ሊሆን የሚችለው
ከባድ ድንጋጤ ሲጨመርበት ነው
የሰው ልጅ ለእራሱ በጣም የሚመኘው
በአንፃሩ ግን ደግሞ ደጋግሞ ሲያስበው
ፈጽሞ ይሆናል ብሎ የማይገምተው
አይሳካም ብሎ ቀልቡ የነገረው
እየቆየም ሲሄድ ተስፋ ያሰቆረጠው
በህይወቱ ውስጥ ግን ትልቅ ቦታ ያለው
በጉጉት ውጤቱን የሚጠባበቀው
አንድ ብርቱ ድርጊት ወሳኝ ነው የሚለው
ድንገት ሲሰምርለት ምንም ሳያስበው
መሆን የለበትም ያለ እስኪያስመስለው
ድንግጥ ሲል ይታያል ግራ ግብት ሲለው
ሰው የሚለውና እሱም በአይኑ ያየው
እውነት አልመስል ብሎት እያጠራጠረው
አምኖ ለመቀበል ሲለሚቸግረው
ፍጹም ያልጠበቀው ጥሩ እድል ሲገጥመው
በደስታ ተሞልቶ መፈንደቅ ሲገባው
ተመልካችን ሁሉ ግራ እስከሚገባው
ስቅስቅ ብሎ አልቅሶ ፊቱን ያጥባል በእንባው
Leave a Reply