የፍቅር ረመጥ (ነሐሴ 2000)

ምንም ሳያስበው አንድ ቀን በድንገት

ቀልቡን የምትስብ ድንግጥ የሚልላት

በአጠገቡ ብታልፍ መልከመልካም ወጣት

በአይኑ ይሸኛታል በልቡ እያጀባት

ንግግር ሳይኖረው ሰላምታ ሳይሰጣት

ፀባይዋን ሳያውቅ በሩቁ ብቻ እይቷት

ውበት ቁመናዋ እጅግ በጣም ማርኮት

የትዳር ጓደኛው እንድትሆን ሲመኛት

አጋጣሚ ሲያገኝ ጊዜ ሲፈቅድለት

አይጠራጠርም የእሱ እንደሚያደርጋት

ያች ያፈቀራት ሰው ልቡ የፈቀዳት

ባለትዳር ትሁን ፍቅረኛ ይኑራት

ወይም የእሷን ፈቃድ ምንም ሳይጠይቃት

እሱ እንደፈለገ የሚያሽከረክራት

ትዕዛዙን አክባሪ እሽ የሚቀናት

ፍጹም የዋህና ቅን አድርጎ እያያት

የእራሱን ፍላጎት ብቻ በመመልከት

ማፍቀሬን አውጥቼ እኔ ስገልጽላት

ወደደችም ጠላች መቀበል አለባት

በማለት የግሉ የብቻው ሊያደርጋት

እንደ እቃ የእኔ ነሽ ብሎ ሲገልጽላት

ማፍቀር የማትችል ስሜትም የሌላት

ወይም ይህን አርጊ ተብሎ ሲነገራት

ምንም ሳትጠይቅ መፈፀም ያለባት

የሰው አሻንጉሊት አድርጎ ቆጥሮአት

ከእኔ ጋር ተስማምተሽ ትዳር ከመመስረት

የተለየ ሌላ አማራጭ የለሽም ብሎ ሲያስፈራራት

እሷም ይህን ሀሳብ ውድቅ ስታደርግበት

ያለፍላጎቷ በግድ ጠልፎ ማግባት

ስብዕናን መካድ ነው ፍጹም እንስሳነት

ወንጀል እየሰሩ በሰው ስቃይ መርካት

ይህ አረመኔነት ርህራሄ ማጣት

ጭራሽ አይለይም ህሊናን ከመሳት

ጭካኔና በቀል ሆን ብሎ ከመዝራት

በእርጋታ ካየነው ሁሉንም በትግዕስት

ሁኔታዎች ሰምረው ጊዜ ሲፈቅድለት

ሆን ብሎ እያወቀ የፈፀመው ድርጊት

እጥፍ ድርብ ሆኖ ልክ እንደ እግር እሳት

በጣም አስጨንቆ ሰላም አሳጥቶት

ፋታ አልሰጥህ ሲለው ስቃይ ሲበዛበት

ይቆይ እንደሁ እንጂ አንድ ቀን በሂደት

ያለፈ ህይወቱን መለስ ብሎ ቃኝቶት

መፀፀቱ አይቀርም በፈፀመው ድርጊት

የሰዎችን ስሜት እንዲሁም ፍላጎት

በደንብ ሳይረዱ ወይ ሳይሰጡት ትኩረት

እንዲያው በአጠቃላይ በደንታ ቢስነት

እንዲሁም በትዕቢት ማን አለብኝነት

በሀይል አስገድዶ ሚስት ጠልፎ ማግባት

አለአዋቂነት ነው በጣም ከባድ ስህተት

ረመጥ እሳት ውስጥ አይን እያየ መግባት

ማርከሻ የሌለው መርዝ አውቆ መጠጣት

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *