ሰው አገር ሰላም ነው ብሎ በሙሉ እምነት
ያለምንም ሀሳብ በተቀመጠበት
ጭራሽ ለምን እንደሁ በማያውቀው ምክንያት
ሰዎች የእሱን ክፉ ውድቀት ሲመኙለት
ያልሠራውን ሠራህ በማለት ሲከሱት
ሆን ብለው ደጋግመው በነገር ሲወጉት
ፋታ አሳጥተውት ሰላሙን ሲነሱት
ምነው ባልተፈጠርኩ እስኪል ሲያበሳጩት
ስቃዩን አብዝተው ተስፋ ሲያስቆርጡት
በመሸነፍ ስሜት መላ ቅጥ ጠፍቶበት
የዉሸት ሳቅ ይስቃል ሳያስበው ድንገት
ከዚያም መለስ ብሎ ጊዜ ሳይወስድበት
የገዛ ድርጊቱ በጣም አስገርሞት
ለካስ እንደዚህ ነው ወዶ አይስቁም ማለት
አንጀት እያረረ ፈገግታ ማሳየት
በማለት በልቡ እራሱን ታዝቦት
ምንም ጊዜ ሳይወስድ በመጽናናት ስሜት
ውስጣዊ ስሜቱን ሰዎች ካወቁበት
ደካማ ነው ብለው እንዳይታዘቡት
ወይም የማይወዱት ሊያዩት የማይፈቅዱት
ሁኔታው አይተው ጮቤ እንዳይረግጡበት
ብሶቱን አፍኖ እምቅ አርጎ ይዞት
ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት
ፍጹም ደስተኛ መስሎ ለመታየት
ሳቅና ፈገግታ ፊቱን አፍክተውት
እራሱን አታሎ ሌሎችን ሲያሳስት
እንዲያው በአጠቃላይ ያለምንም ሀፍረት
ያልሆነውን ሆኖ ሲቀርብ እሌሎች ፊት
በጣም ያሳዝናል የዚህ አይነት ፍጥረት
ፍጹም ወሰን የለሽ ይሉኝታ ቢስነት
ሌላ ጊዜ ደግሞ ስናየው በቅርበት
የሆነውን ሁሉ በጭራሽ ረስቶት
ስሜት የሚነካ ወይ አሳዛኝ ክስተት
ምንም ሳያስበው ድንገት ሲደርስበት
በድንጋጤ ሀይል ማስመሰሉን ትቶት
እንባውን መቋጠር በፍጹም ተስኖት
ገንፍሎ ጉንጩ ላይ ሲፈስስ እንደ ጅረት
በውስጡ ያለውን እውነተኛ ስሜት
ሀዘኑን ፈንቅሎ ስለሚያወጣለት
እርካታ ያገኛል የመንፈስ ነፃነት
Leave a Reply