ዛሬ በዚህ ዘመን ስንፍና ነግሶብን
በስሜት ተገፍተን ማስተዋል ተስኖን
ጥሩውን ከመጥፎ መለየት ሲያቅተን
ከኛ ለየት ብሎ የሚታየንን ሰው
ቀረብ ብለን እንኳን በደንብ ሳናጠናው
ምንም ሳናስተውል ሳናውቅ ማንነቱን
የአስተሳሰብ አድማስ የአላማ ጽናቱን
ፈጽሞ ሳንፈትሽ የሙያ ብቃቱን
እንዲሁ በሩቁ ሳናይ ስብዕናውን
በመሰለኝ ብቻ እንፈርጀዋለን
እንዲህ ነው ለማለት እንቸኩላለን
እሱ የማያውቀውን ስም እንሰጠዋለን
በእራሳችን መስፈርት በመመዘኛችን
የእኛን አስተሳሰብ ያልተቀበሉትን
ስህተት ሰርታችኋል አርሙ የሚሉንን
ወይም እኛን ቀርበው የማይሰግዱልንን
እንደ መጥፎ ጠላት እንቆጥራቸዋለን
በመጸከላቸው ልዩነት እንዳለ ጭራሹን ረስተን
ሁሉንም በጅምላ በአንድ አይን እናያለን
ጠለቅ ብሎ ላየው በደንብ ላስተዋለው
ሌሎችን አይመስልም ሁሉም ሰው ልዩ ነው
የራሱ የሆነ የግል ባህሪ አለው
እሱን እሱ ብቻ እንዲሆን ያረገው
Leave a Reply