ይች ናት እግሬ የማይታይባት ሰው በሰውነቱ
የሚፈረጅባት በዘሩ በቋንቋው ወይ በሃይማኖቱ
ከቀየው ተገፍቶ የሚባረርባት ታይቶ ማንነቱ
ይች ናት አገሬ!
ፍትህ በአደባባይ የሚነፈግባት
የተበዳይ ጩኸት የማይሰማባት
ወንጀለኛ ዳኛ ሆኖ የሚያጏራባት
ይች ናት አገሬ!
ባልስልጣናቷ የሚያሽሞነሙኗት አድጋለች እያሉ
በኑሮ ውድነት የሚጠበስባት ተራው ዜጋ ሁሉ
ያለምንም እክል ከቤት ወጥቶ መግባት
እንደ ትዓምር ነገር የሚቆጠርባት
ይች ናት አገሬ!
የነፃነት ቀንዲል ተብላ የተጠራች
ለሰው ልጆች መብት በአለም ዙሪያ ሁሉ ጥብቅና የቆመች
ቅኝ የተገዙትን ዓርነት ለማውጣት ዋጋ የከፈለች
በዚህ በእኛ ዘመን ይህ ሁሉ ተረስቶ ሁሉም ተቀያይሮ
በትውልድ ትስስር የታነፀ አንድነት ከውስጥ ተቦርቡሮ
መገዳደል ሆኗል የምስኪን ዜጎቿ የእለት ከእለት ኑሮ
ይች ናት አገሬ!
ከልብ የማፈቅራት የእኔ ውድ አለኝታ
ሁሌ የምመኝላት ሰላምና ደስታ
አልጠራጠርም ይህ ማዕበል አልፎ
እንደምታበራ ጨለማው ተገፎ
Leave a Reply