Tag: Belay Zeleke

  • በላይ የቆመበት የታሪክ ከፍታ (ሰኔ 2000)

    ስንቱ ሲፈረጥጥ ሲሸሽ አገር ጥሎ

    የአገሬ ዳር ድንበር የህዝቧም ነፃነት ጠባቂ ነኝ ብሎ

    አባ ኮስትር በላይ የሶማን በርሃ መኖሪያው አድርጎት

    አምስት አመት ሙሉ ለጣሊያን ሰጥቶታል ተገቢውን ቅጣት

    በአገር በወገኑ ለሚመጣ ሁሉ ህይወቱን

    ለመስጠት እንደማያቅማማ

    ጠላትን ሰቅዞ መውጫ መግቢያ እንዲያጣ ማድረጉን ስስማ

    ፍንትው ብሎ ታየኝ በላይ የቆመበት ያ የታሪክ ማማ

  • በላይ ልዮ ጀግና (ሰኔ 2001)

    ስብዕና የሚነካ ጥቃት ሲደርስበት

    በአገር በወገኑ ጉዳይ ሲመጡበት

    ተጋፍጦ የሚቆም በድፍረት ፊት ለፊት

    አገሬ አፍርታለች እልፍ አዕላፍ ጀግና

    ለነፃነት ያለው ፍቅር የሚያስቀና

    የሶማው አንበሳ የጦር መድሃኒቱ

    ምስክር አይሻም ስለ ጀግነቱ

    ልክ እንደ ገድል ነው ጠቅላላ ህይወቱ

    አባ ኮስትር በላይ ስስት የማያውቀው

    ይግባኝ ጠይቅ ቢሉት የሞት ፍርድ ፈርድው

    የድራማው ውጤት ቀድሞ ስለገባው

    ፍጹም ሳያቅማማ አንገቱን ሰጣቸው

  • አገር ሲከሽፍ (ህዳር 2001)

    ሁሌም ስለ አገሬ ሳስብ ሳሰላስል

    የዚያ የበላይ ነገር ድቅን ይልብኛል

    በዱር በገደሉ እንዳልተዋደቅ ለአገሩነፃነት

    ወገኔ ያላቸው የእገሩ ልጆች ፍትህን ነፈጉት

    የጀግኖቹን ጀግና የአገርን አለኝታ

    ያላግባብ ሰቅሎ መመለስ ውለታ

    እንደ አገር የመክሸፍ የታሪክ ድብታ

    መለያችን ሆኗል ካልታረቅን ጌታ

  • በላይ የኔ ነው (መጋቢት 2009)

    አባ ኮስትር በላይ የሰው መውደድ ያለው

    ካለፈም በሁዋላ ወዳጁ ብዙ ነው

    ይኸው ከሞተ እንኳን ሰባ እመት ቢያልፈውም

    ህዝቡ ለእሱ ያለው የጠለቀ ፍቅር መብረጃ የለውም

    ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ የድል ታሪኩን ለእራስ ለመጠቅለል

    በሊህቃን መሀል የእኔ ነው የእኔ ነው በሚል ፍልሚያው ጦፏል

    ባለበት ቢሰማ ይህ ትውልድ ሌት ከቀን ተግቶ እንደሚሯሯጥ

    ሊያስገባው ፈልጎ ለእሱ የማይመጥን የዘር ከረጢት ውስጥ

    ጥርጥር የለውም በመቃብሩ ውስጥ እንደሚገላበጥ

  • የሞራል ከፍታ (ህዳር 2007)

    ለምድራዊ ቁሶች ምንም ግድ የሌለው

    በሞራል ከፍታው ክብር የተላበሰው

    አባኮስትር በላይ የጦር ባለሙያው

    የአገርን ነፃነት በትግሉ አስከብሮ

    የጀግንነትን ጥግ እያሳየ ኖሮ

    መሬትን ወደታች በንቀት እያያት

    ለኢትዮጵያ እናቱ ከልብ ለሚወዳት

    አንገቱን ሰጥቷታል ያለምንም ስስት

  • የሚአሸብረው ሥም (ግንቦት 2007)

    ጅግናው አባኮስትር የሶማው አንበሳ

    በአገሩ ጉዳይ ለነፍሱም አይሳሳ

    ጠላት እሱን በአካል እይቶት ይቅርና

    ብርክ ነው የሚይዘው በላይ ሲባል ገና

  • በላይ ላይ መጨመር (ታህሳስ 1994)

    ሰላቶ ቢቸናን በእጁ ውስጥ ሊያስግባ በደንብ ተዘጋጅቶ

    ሲያደባ ቆይቶ ሁለገብ ወረራ ሳይታሰብ ክፍቶ

    ጀግኖች ተጠራርተው ወጥተው ከቀያቸው

    አባኮስትር በላይ በአስቸኳይ ለሁሉም ስምሪት ሰጥቷቸው

    በፍፁም ጀግነት አትንኩኝ ባይ ወኔ እየተፋለሙ

    ጥቃቱን መክተው ወራሪውን መንጋ አንድ በአንድ ሲለቅሙ

    ምድር በደም ቀልማ የጠላት አስክሬን ሲረፈርፍባት

    ወገን ድል ለማድረግ በተቃረበበት በዚያች ቀውጢ ስአት

    ከመካከላቸው ጀግኖች አንዱን መርጠው

    የሞተውን ጠላት ለይተህ ቁጠረው

    ብለው አዝዘውት ገና እንደጀመረ ብዙም ሳይገፋበት

    በጣም ተቸገረ በላይ በላዩ ላይ እየጨመረበት

  • በላይ ከላይ ሲሆን (ጥር 2014)

    ምን ሃሳብ አለበት ምን ይሆናል ፋኖ

    የጦር ምትሃተኛው በላይ ከላይ ሆኖ

  • በላይ ማርና እሬት (ግንቦት 2008)

    አባኮስትር በላይ የጦሩ መድሃኒት

    ለወዳጆቹ ማር ለጠላቶቹ እሬት

    ያንገበግበኛል የሱ በግፍ መሞት

    ሁሌም ፀሎቴ ነው እንዲቀለው መሬት

  • ያለስስት መስጠት (ሐምሌ 2004)

    ስንቱ ባለፀጋ ሀብትና ንብረቱን ለልጆቹ ሲያወርስ

    አባኮስትር በላይ ተጨንቆ የማያውቀው ስለ ምድራዊ ቁስ

    ምንም እድሜው ቢያጥር በግፍ በአደባባይ ህዝብ ፊት ተስቅሎ

    ስምና ሥራውን ትቶ ነው ያለፈው ለድፍን ኢትዮጵያ ያውላችሁ ብሎ