Category: 2017

  • መስጠት (መጋቢት 2017)

    -ጉቦ የፖሊስ ኢንስፔክተር ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ሲንሸራሸር አይቼ

    ስትሰጥ ይሰጥሀል ሆነና ቢሂሉ
    አገልግሎት ላገኝ በሄድኩበት ሁሉ
    አስተናጋቾቼ እጅ እጄን ያያሉ
    እኔም በተራዬ ዝም ብዬ ሳያቸው
    እጅግ ግርም ይላል ነገረ ሥራቸው
    ደንበኛን በሙሉ በደንብ አድርጋችሁ
    ሳትጨብጡ እንዳይሄድ ግዴታ አለባችሁ
    የሚል ቀጭን ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው
    እጄን ከክሴ ውስጥ ማውጣት ሲቃጣቸው
    በጣም አበሳጭቶኝ አይናውጣነታቸው
    እልም ብዬ ጠፋሁ ቢሮ ውስጥ ጥያቸው

  • የፖለቲካ ሞት (የካቲት 2017)

    የፖለቲካ ሞት ብሎ ሰው ሲናገር
    ትርጉሙ ፈጽሞ አይገባኝም ነበር
    ለካስ መተፋት ነው ተንቆ መወርውር
    ያለምንም ሰሚ ሞትላይቀር ማንቋረር

  • እንባ (መጋቢት 2017)

    የአብሮ አደጌ አፈራ እሸቱ ቀብር ላይ የታዘብኩት

    ሀዘን ምናባቱ የሰው ቅስም ይሰብራል
    ፊትን በእንባ አርሶ አንጀትን ያቆስላል
    እንባስ ወጥቶ ፈሶ ደርቆ ይታጠባል
    ስሜት ነው ታምቆ ቆሽትን የሚያቃጥል

  • ልጅ ወላጅ ሲያስተምር (ታህሳስ 2017)

    እዚህ አሜሪካ ወገኖቻችንን ሳያቸው በቅርበት
    ሁሌም ይገርመኛል ከልጆቻቸው ጋር ያላቸው ተግባቦት

    በቋንቋ በራዕይ በአስተሳሰብ ሁሉ
    ልጆች ከወላጆች በጣም ይለያሉ
    አብረው አየኖሩ ልጄ ወላጆቼ እየተባባሉ
    የሁለት አለም ሰው መስለው ይታያሉ

    ወላጆች ተነስተው በፈረንጅ ቋንቋ እንድ ነገር ሲሉ
    ልጆት ቶሎ ብለው እርምት ይሰጣሉ

    ምን ነካህ አባዬ ምን ነካሽ እማዬ
    ስንቴ ነገርኳችሁ እንደዚህ አይደለም የሚባለው ብዬ

    እያሉ ንትርክ ጭቅጭቅ ሲፈጥሩ
    ግራ ግብት ይላል በእውነት ነገሩ

    እንዲህ ያለ ዘመን የተገላቢጦሽ ግራ የሚያጋባ
    ልጆች ወላጆችን የሚያስተምሩበት በነጋ በጠባ

  • ተሰዶ መቸከል (ታህሳስ 2017)

    እንዴት ያለ ጉድ ነው እንዲህ ያለ ነገር
    የባህል ጏዝ ይዞ መሰደድ ከአገር

    እሄዱበት አገር ሌት ከቀን ሳይሉ ጠንክሮ እየሰሩ
    የተሻለ ኑሮ የተደላደለ በደንብ እየኖሩ

    አገር ቤት ጥለውት የመጡትን ዘይቤ
    የሙጥኝ አልለቅም አይወጣም ከልቤ

    ብሎ የመኖሪያ የሆነውን አገር ለመልመድ መቸገር
    በመንፈስ አገር ቤት እየዋሉ ማደር
    ሌላ ምን ይባላል ከመቸከል በቀር